ፈጣሪዋ በዕንጨት መስቀል ላይ ተዘርግቶ ተሰቅሎ በአየችው ጊዜ ፀሐይ ጨለመች እርሱም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣትን ለባዊት ነባቢት የሆነች ነፍሱን ከሥጋው ለያት ሐዋርያ ጴጥሮስ በሥጋ ምውት ሲሆን በመለኮት ሕያው ነው እንዳለ ነፍሱ ከመለኮት ሳትለይ ከሥጋ ተለየች በዚያ ጊዜ ሥጋ ከመለኮት ሳይለይ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነበር፡፡
እንዲሁም ነፍስ ከመለኮት ጋራ አንድ ሁና እሥረኞች ነፍሳትን ትፈታቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች፡፡
እርሱ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ ያለ ልዑለ ባሕርይ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ ያለ ለእርሱም ምስጋና የክብር ክብር ገንዘቡ የሆነ ራሱን ሠውቶ አዳነን፣ የመንግስቱን ደጆች በፈሳሽ ደሙ ከፈተልን፡፡
ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳለ የእግዚአብሔር ታላቅ የማዳን ሥራ ለባሕርያዊ ደግነቱ የተገባ ነው፡፡ አንድ ንጉሥ የመሠረተው ከተማ ወይም የሠራው ቤት ከጠባቂዎቹ ስንፍና የተነሣ በሽፍታ ቢጠቃና ቢወረር ሽፍታውን ተበቅሎ ይዞታነቱን ያጸናል እንጂ በጠላት በመወረሩ ምክንያት አይተወውም፡፡ የአብ አካላዊ ቃልም የእጁ ሥራ የሆነውን የሰው ዘር ጠፍቶ እንዲቀር አልተወውም፤ ሞትን የራሱን ሰውነት ለሞት አሳልፎ በመስጠት ሲያስወግድ፣ ለሰው ተሰጥቶት፣ ነገር ግን ሕጉን በመተላለፉ ምክንያት አጥቶት የነበረውን ሁሉ በኃይሉና በሥልጣኑ መለሰ፡፡
ይህንንም በመንፈሰ እግዚአብሔር የተቃኙት የመድኀኒታችን አገልጋዮች የጻፏቸው ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ በማለት ያረጋግጡልናል፡፡ ‹‹ይህን ስለ ቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፣ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፣ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ፡፡›› 2 ቆሮ 5÷14-15
በመቀጠልም ሌላ ማንም ሳይሆን ራሱ የእግዚአብሔር ቃል ለምን ሰው መሆን እንዳስፈለገው ምክንያቱን ይነግረናል፡- ‹‹ሁሉ ለእርሱ የሆነና ሁሉም በእርሱ ለሆነ ለርእሱ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ተገብቶታልና፡፡›› ዕብ. 2÷9 ይህም ማለት ሰውን ከጀመረው ጥፋት መልሶ ሕይወትን መስጠት ጥንቱን ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ቃል በስተቀር ለሌላ ለማንም ተገቢ አይደለምና፡፡
አካላዊ ቃል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደው እንደ እርሱ ሰዎች ለሆኑ ሥጋውያን ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ ነበር፡፡ ሐዋርያው ‹‹ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱም እንዲሁ በሥጋና በደም ተካፈለ፤ በሞቱ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ይሽረው ዘንድ፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፤ በሕይወታቸው ዘመን ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ ያወጣ ዘንድ›› ዕብ. 2÷14-15 በማለት እንደገለጸው፡፡ የራሱን ሰውነት በመሰዋት በእኛ ላይ የነበረውን ሕግ (ትሞታለህ የሚለውን) በመፈጸም አስወገደልን፡፡
Read more