ጾምና ጥቅሙ
ከሊቀ ጉባዔ ቀለመወርቅ ውብነህ
ጾም ለተወሰነ ሰዓት ከሁሉም ምግብ መከልከል፣ ሁሉንም ምግብ መተው ሲሆን ለተወሰነ ቀናት ማለት የጾሙ ቀናት እስኪያልፍ ድረስ ከተወሰኑ ምግቦች መከልከል የተወሰኑ ምግቦችን መተው ነው፡፡ ይህም ጥሉላትን ፈጽሞ መተው፣ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጾም ከጥሉላት ምግቦች መከልከል ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጆችን ከሚጎዳ ነገር ሁሉ መከልከልና ለሌሎች መልካም ሥራ መሥራትንም ይጨምራል፡፡
ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ የሆነ ዝምድና እና ጥብቅ ቁርኝት አለው፡፡ ጾም የራሱ የሆነ ሕግጋትና ሥርዓት ስለአለው ጾም ለምን እንደሚጾም፣ ለማን እንደሚጾም፣ መቼ እንደሚጾም፣ እንዴት እንደሚገባና እንዴት እንደሚወጣ ለይቶ የሚያሳውቅ የራሱ የሆነ ሕግና ደንብ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ጾም በብሉይ ኪዳን ከፍተኛ ቦታ የነበረው ሲሆን፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት /ጊዜ/ ወራት እህልና ውኃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ /ዘፀ.34፥28/ በሰው ልጆች በደልና ኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መቅሠፍት /መዓት/ የሚመለሰው /የሚወገደው/ ሕዝቡ በጾምና በጸሎት ሲለምኑትና ሊማልዱት እንደነበር /ዮናስ.2፥7-10/ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡እንደ ቅዱስ ጴጥሮስና እንደ ቆርኔሌዎስ ማለት ነው፡፡ /የሐ.ሥራ 10፥3-9 ለተወሰነ ሰዓትም ከቆዩ በኋላ ጿሚው የሚበላው ዳንኤል በጾመ ጊዜ እንዳደረገው ከቅባት ነጻ የሆነ ምግብ ነው፡፡ “በዚያን ወራት አኔ ዳንኤል ሦስት ሣምንት ሙሉ ሳዝን ነበርኩ፡፡ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፡፡ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፡፡ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም ይላል፡፡ /ዳን.10፥2-3/
ጾም ለነፍስ ብቻ ሳይሆን ለሥጋም መድኀኒት እንደሆነ ጥቂት ነጥቦችን እናነሳለን፡-
ጾምና ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳላቸው ለመረዳት በጥንት ዘመን በተለያዩ ሁኔታዎች ሊደርሱ የነበሩ ችግሮች እንዳይደርሱ ጾምና ጸሎት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው ለምሳሌ፡-
- ጾም እድሜ እንዲያረዝም፤ ሕዝቅያስ የባለው የይሁዳ ንጉሥ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም ረገድ በትክክል ይራመድ ስለነበር፣ የመሞቻው ጊዜ የተቃረበ በመሆኑ ቤቱን እንዲያስተካክል በነቢዩ ኢሳይያስ አማካይነት የእግዚአብሔር ትእዛዝ ተናገረው፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስም የመሞቻው ጊዜ ሲነገረው በመሪር ልቅሶና ሐዘን ልመናውን ለእግዚአብሔር ስላቀረበ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ፣ ልመናውን በመቀበል እድሜው በአሥራ አምስት ዓመታት እንዲራዘም ያደረገለት መሆኑን በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ. 20፥ ይመለከቷል፡፡
- ጾም በጠላት ላይ ድል እንደሚያጎናጽፍ አርጤክስስ በተባለው በፋርስ ንጉሥ ዘመነ መንግሥት ሐማ የተባለው ሰው ከፍተኛ ሹመት/ሥልጣን/ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ስለዚህ ሐማ ለተባለው ሰው የቤተ መንግሥቱ አሽከሮች ሁሉ እንዲሰግዱለት የንጉሡ ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ ከቤተ መንግሥቱ አሽከሮች መካከል መርዶክዮስ የተባለው አይሁዳዊ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አልሰግድም በሚል የጸና እምነት እንደሌሎቹ የቤተ መንግሥት አሽከሮች የማይሰግድለት መሆኑን ባወቀ ጊዜ ይህ ሐማ የተባለው ባሥልጣን ንጉሡን አስፈቅዶ በግዛቱ ይገኙ የነበሩት ነገደ አይሁድ/የአይሁድ ወገኖች/ በሙሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ በዚህ ምክንያት መርዶክዮስና በዚያን ጊዜ ንግሥት ሆና የነበረችው አስቴር የተባለችው የመርዶክዮስ የአጎት ልጅ ለአይሁድ ሕዝብ በሙሉ ጾምንና ጸሎትን ዐወጁ፡፡ ሕዝቡም ዐዋጁን ተቀብሎ በጾመና በጸለየ ጊዜ ለመርዶክዮስ አዘጋጅቶት በነበረው ግንድ ላይ ሐማ ራሱ እንዲሰቀል ከመደረጉም በላይ መርዶክዮስ ከንጉሡ ቀጥሎ ያለውን ከፍተኛ ሹመትና ክብር ተሰጥቶት ሐማ ያስተላለፈው ውሳኔ እንዲሻር ተደረገ፡፡ ሁኔታው በዚህ ብቻ ያቆመ ሳይሆን፣ የሐማ አሥር ልጆችና የአይሁድ ሕዝብ ጠላት የሆነ ሰው ሁሉ እንዲገደል ተደርጓል፡፡ አስቴር 4 – 10፡፡
- ጾም ከነፍስ ብቻ ሳይሆን ከሥጋዊ ሞትም ማዳን እንደሚችል፡፡ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር፣ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም ካለመ በኋላ ሕልሙን ማስታወስ ስላቃተው መንፈሱ ታወከበት፡፡ በዚያ ጊዜ የነበሩትን የባቢሎንን ጠቢባን ሁሉ ሰብስቦ ሕልሙን እንዲነግሩት ጠያቃቸው፡፡ እነሱም ህልሙን ነግሮአቸው ለመተርጎም ካልሆነ በቀር ምን ህልም እንዳለመ ሊነግሩት የማይችሉ መሆናቸውን በገለጡለት ጊዜ ሁሉም ተሰብስበው እንዲገደሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ በዚህ ጊዜ ነቢዩ ዳንኤል የንጉሡን ጥያቄ ለመመለስ ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ከጠየቀ በኋላ ከጓደኞቹ ከአናንያ፣ ከአዛርያና፣ ከሚሳኤል ጋር ሆነው በመጸለይ ህልሙ ከነትርጓሜው ለዳንኤል ተገለጸለት ለንጉሡ በመናገሩ ለወገኖቹ ለአይሁድ ሕዝብ ዕረፍትን ከማስገኘቱም በላይ የባቢሎን ጠቢባንን ከሞት ፍርድ እንዲድኑ አድርጎአቸዋል፡፡ /ዳን.ም2፥/
- ጾም በክፉ ሥራ ምክንያት ከታዘዘ መቅሰፈት እንደሚያድን የነነዌ ከተማ ሰዎች በክፉ ሥራቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶ ስለነበር፣ በንስሐ የማይመለሱ ከሆነ፣ ከተማቸው ከሦስት ቀኖች በኋላ የምትገለበጥ መሆንዋን የሚገልጽ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ነቢዩ ዮናስ መጣ፡፡ ይህንኑ የእግዚብሔር ውሳኔ ነቢዩ ዮናስ ለነነዌ ሰዎች በነገራቸው ጊዜ በንጉሡ አዋጅ መሠረት ሕዝቡ ራሱን ዝቅ አድርጎ በጾምና በጸሎት የእግዚብሔርን ይቅርታ ስለለመነ፣ ሊደርስ የነበረው ቅጣት/መቅሠፍት/ ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ ዮናስ.3፥
- ጾም ከእሥር እንደሚያስፈታ፡፡ ንጉሥ ሄሮድስ በዘመነ ሐዋርያት አይሁድን ለማለዱት ሲል የቅዱስ ዮሐንስን ወንድም ቅዱስ ያዕቆብን ከገደለው በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስን ደግሞ ለፍርድ ለማቅረብ አስቦ ወደ እስር ቤት በመላክ በአራት ጠባቂዎች እንዲጠበቅ አደረገው፡፡ በዚያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ አጥብቃ በመጸለይዋ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ከእስር ቤት ያወጣው መሆኑን፣ በሐዋርያት ሥራም 12፥1-10 ተመልክቷል፡፡
የጾምንና የጸሎትን ኃይል ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስረዳ እንደዚህ ዓይነቱ ርኩስ መንፈስ በጾምና በጸሎት አማካይነት ካልሆነ በስተቀር አይወጣም ብሏቸዋል፡፡ /ማቴ.17፥21/ጾም የራስን በደል አምኖ፣ ጸድቶ፣ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በድያለሁ ማረኝ በማለት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ለማግኘት የሚረዳ ታላቅ መሣሪያ ነው ሳሙ.7፥5-6፡፡ የጾም ጥቅሙና አገልግሎቱ በጥንቱ ዘመን ከአበው ጀምሮ በግልጽ የታወቀ እንደ ነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት በሚገባ ያስረዳሉ፡፡ በሙሴ ዘመን ጾም የተገለጸው የተቀደሰ ጉባዔ ወይም ራስን ማስጨነቅ በሚል አነጋገር ነው /ዘሌ.16፥19፣ 23፥27፣ ዘኁ.29፥7 ጾም የሚጾመው ከእግዚአብሔር ሊያገኙት የሚገባ ጸጋንና በረከትን፣ ይቅርታንና ምኅረትን፣ ለማግኘት ነው፡፡ ሙሴ በደብረ ሲና 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሞ በግብር አምላካዊ የተጻፉ ዐሥርቱ ቃላትን ተቀብሏል /ዘፀ.34፥28፣ ዘዳ.9፥9-15/፡፡
ጾም ጸሎትና ስግደት፣ ጾም ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የሚነጋገሩበት ቋንቋ የሚገናኙበት ድልድይ ወይም መሰላል በመሆኑ በንጽሕናና በቅድስና የሚፈጸም ሥርዓት ነው /ነህ.9፥1-3/፡፡ ጾም ከተንኮልና ከክፋት ከመሰላሰሉት የሰይጣን ሥራዎች ሁሉ ርቆ ስለ ራስና ስለ ሕዝብ ሥርየት ኃጢአትን ሰላምና በረከትን ለመለመን፣ ፊትን ወደ እግዚአብሔር ማቅናት ነው፡፡ /ዳን.9፥1-19፣ 6፥18/ የጾምና የጸሎት ውጤትም በንጹሕ ልቡና እና በቀና ኅሊና ለሚጾመው ሰው በመላእክት አማካይነት ይገለጻል /ዳን.9፥20/፡፡ ጾም ወደ እግዜአብሔር አቤቱታ የማቅረብያ መንገድ በመሆኑ ያልታሰበ ችግርና ፈተና ሲያጋጥም፣ ሕዝብ እንዲጾም፣ እንዲጸልይ፣ በእግዚአብሔር ፊት ራሱን እንዲያዋርድ አዋጅ ይነገራል፡፡ /ዕዝ.8፥21፣ አስ.4፥3፣ ኤር.37፥9፣ ኢዮ.1፥13-14/ ይመለከቷል፡፡
የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት እሑድ ቅድስት ይባላል፡፡
ይህም ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና የሚያወሳ ነው፡፡ ቅዱስ እግዚብሔር የረከሰውን ዓለም ለመቀደስ በመጣ ጊዜ ከጥምቀቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጸመው ተግባር ለሰው ልጅ ቅድስና ሲል፣ እንደ ሰው ገዳም ገብቶ መጾም፣ መስገድ፣ በጸሎት መትጋት ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ወደሚባል ምድረ በዳ ሄዶ በዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል፡፡ ማቲ.4፥1-2፡፡ 40ውን ቀን ጾመ ቢባልም እህል ውኃ ሳይቀምስ ነው እንጂ እንደኛ ጾም ውሎ ማታ እየተመገበ ሲደክም ውሎ ሌሊት አርፎ እያደረ አይደለም፡፡ /ሉቃ.4፥2/ ሳይበላና ሳይጠጣ 40 ቀንና 40 ሌሊት ሙሊ በመጾም ክብረ ጾምን አስተምሮናል፡፡
ቅድስት
ቅድስት ማለት የተቀደሰች፣ የተባረከች፣ ንጽሕት ማለት ነው፡፡ ጾምን ቀድሱ ጉባኤውን አውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፡፡ ኢዮ.1፥14 በኢዩኤል አፍ የተናገረ ቅዱስ እግዚአብሔር የጾማት ጾም ስለሆነች ቅድስት ትባላለች፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዲያብሎስን ፈተና ድል ለመንሳት በቅድስት ከተማ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ጫፍ የቆመባት ዕለት በመሆኗ ቅድስት ትባላለች ማቴ. 4፥5፣ ዮሐ.10፥22-23፡፡ ቅድስት የቤተ ክርስቲያን ማዕከል የመቅደስና የቅኔ ማኅሌት ሁለተኛው ክፍል የምእመናን መጸለያ፣ የካህናት ሥጋ ወደሙ ማቅረቢያ፣ መቅረዝና የዕጣን መሠዊያ የተቀደሰች የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት ዘፀ.23፥33-35፣ 30፥6፣ ዕብ.9፥2፡፡
ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከቅዱሳን ይልቅ የተቀደሰች፣ ከከበሩ የከበረች መቅደስ ኦሪት ቅድስት 20 ክንድ ቅዱሳን የሚባሉት መቅደስና ቅኔ ማኅሌት 40ው ክንድ ናቸው፡፡ ቅድስት፣ ዕለተ ሰንበት እግዚአብሔር ሰባተኛይቱን ቀን ባረካት፣ ቀደሳት ዘፍ.2፥3፣ ዘፀ.20፥8፡፡ ቅዱስ ያሬድም ሰንበትየ ቅድስትየ እንተ አዕረፍኩ እምኲሉ ግብርየ ይቤ እግዚአብሔር ብሏል፡፡ ቅድስት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ መዝ.95፥5 በእነዚህና በመሳሰሉት ሁለተኛዋ ሳምንት ቅድስት ትባላለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
{flike}{plusone}