የስቶክሆልም መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ የሰበካ አስተዳደር ምርጫ አካሄደ
ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰ/ምዕራብ አውሮፓ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ
በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰ/ምዕራብ አውሮፓ ሀ/ስብከት የስቶክሆልም መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ እና ሥራ አስኪያጁ መጋቤ አእላፍ ተወልደ ገብሩ እንዲሁም የአጥቢያው ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እና ምእመናን በተገኙበት የካቲት 02 ቀን 2006 ዓ.ም. በ S:t Jacobs Kyrka, Stockholm, Sweden ባደረገው አጠቃላይ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ቃለ ዓዋዲ ሕግና በሀገሩ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት:- መላከ ብርሃን አባ ገብረ ጊዮርጊስ ካሳዬ አለሙ፣ ዲ/ን ተሻለ ቢያዝን፣ ዲ/ን ኪሮስ አብርሃ፣ ታሪኩ ተመስገን፣ ይሁን ድሌ፣ በላይነሽ ገዝሄ፣ ጸደይ ሀጎስ፣ ታጠቅ ፍቃዱ እና ተስፋየ ገ/ማርያም የአጥቢያው ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ሆነው እንዲያገለግሉ በሙሉ ድምጽ መርጦ ሰይሟል።
የአዲሱ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ በጠቅላላ ጉባኤው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን አባ ገ/ጊዮርጊስ ካሳዬ አለሙ ሰብሳቢነት በቃለ አዋዲ ደንብ እየተመራ:-
- የአጥቢያው አገልጋይ ካህናትና ምእመናን የቤተክርቲያኗን ሕግ፣ ሥርዐት እና ቀኖና ጠብቀው እንዲያገለግሉና እንዲገለገሉ እንዲያደርግ፣
- የተዘጋውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በሕግ አስከፍቶ የተለመደውን መንፈሳዊ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል፣
- የቃለ ዓዋዲን ደንብ ከሀገሩ የሃይማኖት ተቋማት መመሪያ ጋር በማጣጣም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኗን የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ በማዘጋጀትና ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቦ በማስጸደቅ በሥራ ላይ እንዲያውል የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል።
የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል
ብፁዕነታቸው አያይዘውም ለቀድሞው የሰበካ አስተዳደር ባስተላለፉት መመሪያ የቀድሞው የሰበካ አስተዳደር ኮሚቴ በአጥቢያው ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ መመረጡን አውቆ ይህ ምርጫ ከተካሄደበት የካቲት 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነቱ የተነሳ መሆኑን እና በእጁ የሚገኙ ከማህተም ጀምሮ ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያኗን ንብረቶች ለአዲሱ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ በጥንቃቄ እንዲያስረክብ በአጽንኦት አሳስበዋል። በመጨረሻም ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን የአጥቢያ ቤተክርስቲያኗ ካህናት እና ምእመናን ከአዲሱ የሰበካ አስተዳደር ኮሚቴ ጋር በመሆን የሰላምን መንገድ ተከትለው፣ መለያየትን አስወግደው፣ በፍቅር እና በአንድነት እንዲያገለግሉ እና እንዲገለገሉ፤ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት አክብረው እንዲያስከብሩ አሳስበዋል።
የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል
{flike}{plusone}