ታሪክ

የመ/ጸ/ቅ/ሥ/ ቤተክርስቲያን አጭር የምስረታና የአገልግሎት ዘመን ትውስታ

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ታቦተ ሕግ ቅድስት ሀገር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት ገዳም በልዑል እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልንና በቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ አማካኝነት ጥር 12 ቀን 1998 ዓ.ም. ወደ ሀገረ ስዊድን ስቶክሆልም ከተማ በክብር ደረሰ። ይህንንም ተከትሎ እ.ኤ.አ. ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም. (ጥር 29 ቀን 1998 ዓ.ም.) በተደረገው ስብሰባ አስራ አንድ አባላት ያሉት የሰበካ ጉባኤ አስተባባሪ ኮሚቴ ተመረጠ። ይህ በመሆኑም ቤተክርስቲያኑ የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት እየተስፋፋ መሄድ ጀመረ።

ነገር ግን በዚህ ቤተክርስቲያኑ የአገልግሎቱን አድማስ ለማስፋት በሚጥርበት ጊዜ ሁነኛ ፈተና እየገጠመው መጣ። እንደሚታወቀው በወቅቱ በነበረው ታሪካዊ  ክስተት በውጭ ሀገር ሌላ ሲኖዶስ ተቋቁሟል ተብሎ የታወጀበት ወቅት ስለነበር በውጭ ሀገር ባለው ህዝበ ክርስቲያን መካከል አለመረጋጋት መፈጠሩ ይታወሳል። በወቅቱ የነበሩት የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አስተባባሪዎች ቅዱስ ሲኖዶስን በተመለከተ የተነሳው ችግር በሊቃውንቱ ትምህርትና በሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት እና መመሪያ ለዘለቄታዉ እስኪፈታ ድረስ አገልግሎታችንን በገለልተኝነት መተግብር አለብን በሚል እሳቤ ከሀ/ስብከቱ ውጭ ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጅ ይህ ዓይነቱ አገልግሎት ከቀኖና ቤተክስቲያን ጋር ስለሚፃረር የሰበካ ጉባኤ አስተዳደሩ ከሚያዚያ ወር 1998 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን ምዕራም አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ጋር ግንኙነት በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር የሚገባበትን መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአጥቢያው ሰበካ አስተዳደር የቤተክርስቲኒቱ ሊቃዉንት ከኢትዮጵያ ተጋብዘው ትክክለኛውን የቤተክርስቲያን ትምህርት: ቀኖና እና ትውፊት ለማህበረ ምእመናኑ እንዲያስተምሩ አድርገዋል። ስለሆነም ከነሐሴ 21 – 23 ቀን 2002 ዓ.ም. ከሀገር ቤት በመጡ መምህራን ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተደረገ መንፈሳዊ ጉባኤ በምእመኑ አዕምሮ ውስጥ ሲመላለሱ የነበሩት ቅዱስ ሲኖዶስን የተመለከቱ እና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎች መልስ በማግኘታቸው ጉባኤው ባለቀበት ዕለት በወቅቱ የነበሩት የሰበካ ጉባኤ አስተባባሪዎች መሪነት መምህራኑ ባስተማሩት ትክክለኛ ትምህርት መሠረት የማይሰደድ ፧ያልተሰደደ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በቅድስት ሀገር በኢትዮጵያ እንደሚገኝ ሁሉም በሙሉ እምነት በመቀበላቸው ከነሐሴ 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን ምዕራም አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ እንጦንስ ምክርና ቃለ ምዕዳን እየተመራ በእናት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱን እየፈጸመ ይገኛል።

ከቤተ ክርስቲያኗ ምስረታ ጀምሮ በሚችሉት ሁሉ አስተዋጽኦ ያደረጉ ምእመናንን  ሁሉ እግዚአብሔር አምላክ በቤቱ አጽንቶ የመንግስቱ ወራሾች ያድርግልን። በእነዚህ አባቶች እናቶች ወንድሞችና እህቶች ላይ አድሮ ይህን አገልግሎት እንድናገኝ ላደረገን ልዑል አምላካችን ክብር ምስጋና ይግባው። አሜን።