ጸሎተ ሐሙስ

በሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ

ጸሎተ ሐሙስ ነቢያት በሀብተ ትንቢት በመንፈሰ ትንቢት ‹‹እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት›› /መዝ. 117፥24/ በማለት ትንቢት የተናገሩላት በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ትላልቅ የተባሉ ምሥጢራት የተፈጸሙባት ዕለት ናት፡፡

“እግዚአብሔርም በግብጽ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው ይህ ወር የወሮች የመጀመሪያ ይሁናችሁ የዓመቱም የመጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፡፡ ለእስራኤል  ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ፡፡ የቤቱ ሰዎች ቁጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደነፍሶቻቸው ቁጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ፡፡ የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰዱ በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛ ቀን ድረስ ጠብቁት፡፡ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት፡፡ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቀቡት፡፡ በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ ከመራራው ቅጠል ጋር ይበሉታል ጥሬውን በውኃ የበሰለውን አትብሉ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት ከእርሱም እስከ ጧት አንዳች አታስቀሩ እስከ ጧትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፡፡ ፈጥናችሁም ትበሉታላችሁ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው፡፡ እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ አገር አልፋለሁ… ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁንላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ ለልጅ ልጃችሁም ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ /ዘዳ.12፥1-15/፡፡

 

እስራኤል ይኸንን ሥርዓት በሚፈጽሙበት ዓመታዊ በዓል ዋዜማ ላይ ነበር ሐዋርያቱ ወደ ጌታችን ቀርበው እንዲህ ያሉት “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ?  እርሱም ወደከተማ ወደ አልዓዛር ቤት ላካቸው /ማቴ.20፥6-18/፡፡
 
አስቀድመን የገለጥነው ቃል እስራኤል ዘሥጋ ከሞተ በኩር የዳኑበት የፋሲካ በግ ምሳሌነት የሚያሳይ ነው፡፡
በጉ ነውር የሌለበት የመሆኑ ምክንያት ኀጢአት የሌለበት የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጉን በወሩ በዐሥራ አራተኛው ቀን እንዲሠውት እንደታዘዙ የጌታ ምክረ ሞቱ በዐሥር ተጀምሮ በዐሥራ አራተኛው ቀን ተፈጽሟል፡፡ የበጉ ደም የተቀባበት ቤት ሞተ በኩር አልደረሰም በመስቀሉ ላይ የፈሰሰውን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉ ክርስቲያኖችንም ሞት አይደርስባቸውም፡፡ የበጉን ሥጋ ጥሬውንና ቅቅሉን እንዳይበሉ ጥብሱን እንዲበሉ  ታዘዋል ይህም በእሳት የተመሰለ መለኮት የተዋሐደውን ነፍስ የተለየውን ሥጋና ደም ለምንቀበል ለእኛ ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ነው፡፡
አታሳድሩ ከአንዱ ወደሌላው አትውሰዱት መባሉ ጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ላለማደሩ እና ወደ መቃብር መውረዱን የሚያስረዳ ሲሆን የበላችሁትን አታሳድሩ መባሉ ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን ተረፈ መሥዋዕት አያድርምና ነው፡፡
በጸሎተ ሐሙስ የሚከተሉት ዋና ዋና ምሥጢራት ተፈጽመዋል፡-
 
የማይሻረው፣ ዘላለማዊው፣ ፍጹሙ፣ ኪዳን የተመሠረተበት ዕለት ነው፡፡
እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ኪዳናት የተሻሩ አሉ የማይሻሩም አሉ፡፡ የማይሻሩ ኪዳናት ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ ሙሴ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት፣ ኪዳነ ምሕረት ናቸው፡፡ የተሻሩት የደም ኪዳናት ናቸው፡፡ በደም የተመሠረቱ የብሉይ ዘመን ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳን አምላካዊ ደም ተሽሯል፡፡ በዚች ዕለት በአልአዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጡ፡፡ ከኅብስቱ ከፍሎ አማናዊ ሥጋ ከወይኑ ከፍሎ አማናዊ ደም አድርጎ ባርኮ ቀድሶ አክብሮ እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው እንዲህም አለ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡ /ማቴ.26፥26/ ይህ ሥርዓት የክህነቱንም ሥርዓት የቀየረ ሥርዓት ነው፡፡
ቅዱስና ያለተንኮል ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞች የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል፡፡ እርሱም አስቀድሞ ስለራሱ ኀጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ አይገባውም፡፡ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህንን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጓልና” /ዕብ.7፥27/ ተብሎ የተነገረለት የሐዲስ ኪዳን የክህነት ሥርዐት ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ የነበረው የእንስሳት ደም ተሽሮ አማናዊ የሆነው የክርስቶስ ደም የተተካበት ዘላለማዊ ፍጹም ኪዳን የተቀበልንበት ዕለት ነው፡፡
 
አዲስ ሕይወት አዲስ ዘመን የተመሠረተበት ነው፡፡
ዘመኑ ሥያሜውን ያገኘው በዚች ዕለት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ሥርዓት መሥዋዕት የተሠራበት ዕለት ነው፡፡ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራ አንሥቶ ባርኮ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ማቴ. 26፥26 ስለዚህ ሐዲስ ኪዳን የሚለው ስያሜ በዚች ቀን እንደተፈጸመ ልብ ይሏል፡፡ የቀደመው ኪዳን እርሱም በደም የሆነው መሥዋዕትነት አለፈ በተሻለው የመረጨት ደም እርሱም በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ምክንያት ዘመን ተለወጠ፣ ስያሜውንም አገኘ እርሱም ሐዲስ ኪዳን /ዓመተ ምሕረት/ ነው፡፡ የፍዳ፣ የመርገም፣ የኩነኔ ዘመን አልፎ የምሕረት፣ የነፃነት፣ የድኅነት ዘመን ተተካ፡፡
አገልጋዮቹን የለየበት ዕለት ነው፡፡
የእርሱ ገንዘብ የሆኑ ሐዋርያት እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ይታመኑ ዘንድ አገልግሎታቸውን ያጸናበት የማይገባቸውን ወገኖች የለየበት ዕለት ናት፡፡ ይሁዳ የሐዲስ ኪዳን ሰው አልበረም “በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ፤ ሲበሉም እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ፡፡ እጅግም አዝነው እያንዳንዱ ጌታ ሆይ እኔ እሆንን ይሉት ጀመር፤ እርሱም መልሶ እጁን በወጭቱ ያጠለቀው እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ነው አለ፡፡ /ማቴ.26፥20/ ይሁዳ በዚች ዕለት ከሐዋርየት ተለየ፤ ጌታውን ለሠላሳ ብር አሳልፎ ሰጠ፡፡ ስለዚህ የሐዲስ ኪዳን አገልጋዮች ከፍቅረ ነዋይ፣ ከአድመኝነት፣ ከምቀኝነት የራቁ፣ የተለዩ ለፈጣሪያቸውና ለአገልግሎታቸው የታመኑ እንዲሆኑ ሥርዐት ተሠራ፡፡
ሐዋርያት የተጠመቁበት ዕለት ነው፡፡
እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው ዐሳብ ካገባ በኋላ ኢየሱስ ከራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡” ዮሐ.13፥1-10
ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ሊከላከል ሞከረ፤ ጌታችን እንዲህ አለው “እኔ የማደርገውን አሁን አንተ አታውቅም በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው /ዮሐ.13፥10/፡፡ ጴጥሮስ የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም ባለው ጊዜ የጌታችን መልስ ይህ ነበር “ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” ቁ.9/ በእርግጥም ያልተጠመቀ ከጌታ እድል ክፍል የለውም፡፡ እናም ቅዱሳን ሐዋርያት በእዚህች ዕለት የተጠመቁባት ዕለት ናት፡፡
ማጠቃለያ
ቅዱስ እግዚአብሔር አማናዊ ሥጋውን አማናዊ ደሙን የሰጠባት፣ ለሕይወት ለበረከት እንድንሆን ምሥጢሩን የገለጠባት፣ ምዕመናንን ቅዱስ ሥጋውን በልተው ክቡር ደሙን ጠጥተው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚቀበሉባት፣ የትንሣኤውን ብርሃን በተስፋ የምንጠባበቅባት ዕለት በመሆኗ ይህች ዕለት ለእኛ ለክርስቲያኖች ልዩ የሆነ ትርጉም አላት፡፡ ዕለቷንም የምናከብረው በዚህ መንፈስ ነው፡፡

ምስጋና ይሁን አንድ አምላክ ሚሆን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እስከ ዘለዓለሙ አሜን፡፡