ሰሙነ ሕማማት

በዲያቆን ኅሩይ ባየ

የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት እጅግ የተናፋቂና ተወዳጅ ሳምንት ነው፡፡ በእነዚህ 6 ዕለታት የአምላካችንን ሕማም መከራና ስቃይ አብዝተን የምናዘክርባቸው ዕለታት ናቸው፡፡ የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸዋትዎ መከራ በዓመት አንድ ጊዜ በተወሰኑ ዕለታት የሚታሰብ ሳይሆን በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የምናስበው የዕድሜ ልክ ስጦታ ነው፡፡ ይኸን ሲያስታውስ ሐዋርያው እንዲህ ይላል “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ይህንንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” 1ቆሮ.11፥26፡፡ እውነት ነው ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበትን በዕለተ ዐርብ ስለ እኛ ፍቅር የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋና የፈሰሰውን ክቡር ደም ስንቀበል ሕማሙን ሞቱን ትንሣኤውን እናስባለን፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡” 2ቆሮ.4፥10 በማለት ሞቱን ማሰብ የሕይወታችን መሠረት እንደሆነ የጻፈልን፡፡

በእርሱ ሞት እኛ ሕይወትን እንድናገኝ ሞቱ በቅዱሳን ሕይወቱ ደግሞ ለእኛ ሆነልን 2ቆሮ.4፥12፡፡ ስለዚህ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሰጠንን እርሱን እናመሰግነዋለን፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የድኅነት ትምህርት በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በጥልቀትና በስፋት ተብራርቷል፡፡ ድኅነታችን የፕሮቴስታንቱ ዓለም እንደሚለው በጸጋ ብቻ ያይደለ በእምነትና በምግባር የሚከናወን በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የሚደመደም በተጋድሎ የሚሠምር ነው፡፡

በሰሙነ ሕማማት ደረጃ በደረጃ የሚካሔዱ ሥርዐቶች አሉ እነዚህ ተግባራዊ ሥርዐቶች መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዐይነ ኅሊና እየሳልን በልቡናችን ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ እንከተለዋለን፡፡

በዕለተ ሆሣዕና የቤተ መቅደሱ በር ተዘግቶ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ የሆነው አምላክ በበር ቆሞ “አርኅው ኆኀተ መኳንንት….. መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ” በማለት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ካህናተ አይሁድ የልቡናቸውን በር ቆልፈው አምላክነቱን ክደው እሩቅ ብእሲ እንደሆነ በማሰብ “ደጆቻችንን እንከፍትልህ ዘንድ አንተ ማነህ?” ማለታቸውን ለማስታወስ የዕለቱ ቀዳስያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይሆናሉ፡፡

ከሆሣዕና ማግሥት ከዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ያሉት ዕለታት የራሳቸው ስያሜ አላቸው፡፡

 

ሰኞ፡- መርገመ በለስ የተፈጸመባት ሰኞ ትባላለች፡፡ የዚህም ስያሜ መነሻው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሆሣዕና ቢታንያ አድሮ በማግስቱ ሲወጣ በለስን ተመለከተና ፍሬዋን ሊመገብ ወደደ፡፡ ሆኖም በለሷ ቅጠል እንጂ ፍሬ ስላልያዘች የሚበላ አንዳች ነገር አልተገኘባትም ኢየሱስ ክርስቶስም “ከእንግዲህ በኋላ አንዳች ፍሬ አይገኝብሽ” ብሎ መርገም ያስተላለፈበት ዕለት በመሆኑ መርገመ በለስ የተፈጸመባት ሰኞ ትባላለች፡፡

ማክሰኞ፡- የጥያቄ ቀን ትባላለች በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21፥23 እንደተገለጠው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ተገኝቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ነጋዴዎች ገበታቸውን ገለባብጧል፡፡ ይህን በማድረጉ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ከነገሥታት ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር ተአምራት ማድረግ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? ብለው ጠይቀውታል፡፡ /ማር.11፥7፣ ሉቃ.20፥1-8/ የጥበብ ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር የፈሪሳውያኑን ጥያቄ በጥያቄ መለሰላቸው፡፡ “…..የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበር፤ ከሰማይ ነውን? ወይስ ከሰው? በእግዚአብሔር ፈቃድ ወይስ በሰው ፈቃድ?” አላቸው እነሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም” ብለውታል፡፡ ይህን አውደ ትምህርት ለማሰብ ማክሰኞን የጥያቄ ቀን እንላታለን፡፡ ምክንያቱም በቤተ መቅደስ ረዥም ትምህርት በማስተማሩ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

ረቡዕ፡- ምክረ አይሁድ የመልካም መግዣ ቀንና የእንባ ቀን ይባላል፡፡ ምክረ አይሁድ መባሉ አይሁድና ሊቃነ ካህናት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር መጨረሳቸውን የመልካም መግዣ ቀን መባሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከስምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ ማርያም እንተ እፍረት /ባለሽቱዋ ማርያም/ ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ ይዛ በጸጉሩ ላይ በማፍሰሷ የመልካም መግዣ ቀን ተብሏል፡፡ የእንባ ቀንም መባሉ ማርያም እንተ እፍረት በእንባዋ እግሩን በማጠቧ ነው፡፡

ሐሙስ፡- ጸሎተ ሐሙስ፣ ሕፅበተ ሐሙስ፣ የምሥጢር ቀንና የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ ጸሎተ ሐሙስ የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርያነት በጌተ ሴማኒ ሲጸልይ በማደሩ ነው፡፡ /ማቴ.26፥36/ ህጽበተ ሐሙስ መባሉም የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ነው፤ የምሥጢር ቀን መባሉ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቊርባን የተመሠረተበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ መባሉም መሥዋዕተ ኦሪት አልፎ የሐዲስ ኪዳኑ መሥዋዕት ሊሰዋ በመሆኑ ነው፡፡ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ” /ሉቃ.22፥20

ዐርብ፡- የስቅለት ዐርብ መልካም ዐርብ ይባላል፡፡ የስቅለት ዐርብ መባሉ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን ያፈሰሰበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ መልካም ዐርብ መባሉም መስቀል ለሮማውያን የቅጣት ለአይሁድ ደግሞ የእርግማን ምልክት ነበር፡፡ ስለዚህ መስቀል የበጎ ነገር ምልክት ተደርጎ በመሰጠቱ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይፈረድበታል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን የመርገምና የቅጣት ምልክት በሆነው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የምሕረት የድልና የክብር ምልክት ስላደረገው መልካም ዐርብ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ቅዳሜ፡- ቀዳም ስዑር ለምለም ቅዳሜ፣ ቅዱስ ቅዳሜ ትባላለች፡፡ ቀዳም ሥዑር መባሉ ከወትሮው ዕለታት በተለየ ይህችኛዋ ዕለት በጾም ስለምትታሰብ የተሻረች ቅዳሜ እንላታለን፡፡ ለምለም ቅዳሜ መባሏም ካህናቱ የምሥራች አብሳሪ የሆነውን ቄጤማ ይዘው ወደ ምእመናን ቤት ስለሚሔዱ ለምለም ቅዳሜ ትባላለች፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉም በጥንተ ተፈጥሮ ሃያ ሁለቱን ስነ ፍጥረታት ፈጥሮ ያከናወነው በዕለተ ዐርብ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ከሥራው ያረፈበት ዕለት ናት፡፡ በዘመነ ሐዲስም የማዳን ሥራውን አከናውኖ በከርሰ መቃብር አድሮ በአካለ ነፍስም ሲዖልን በርብሮ ተግዘው የነበሩትን ነፍሳት ያወጣበት ዕለት በመሆኑ ቅዱስ /ልዩ/ ቅዳሜ ተብላ ተሰይማለች፡፡

በሰሙነ ሕማማት ማኅበረ ካህናት ምእመናንና ምእመናት በአጸደ መቅደሱ ተሰብስበው ከሥጋዊ ሥራ ርቀው አምላካቸውን በማሰብ ሰፊውን ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡ ስለ ሕማሙ የተተነበዩትን ትንቢቶች የተዘመሩ መዝሙሮች የተመሰሉ ምሳሌዎች የተሰበኩ ስብከቶች የተጻፉ መልእክታትን እያነበቡ እያደመጡ በሰጊድ በጾምና በጸሎት ከነግህ እስከ ሰርክ ይቆያሉ፡፡

ዘመነ ፍዳ ዘመነ ኩነኔ የሰለጠነበትን ዓመታት ለማስታወስ ካህናቱ በአገልግሎታቸው ጊዜ ጥቁር ይለብሳሉ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባለው ሁሉ የላመ የጣመ ከመመገብ ይቆጠባሉ፡፡ ንግግራቸውን አካሔዳቸው፣ አመጋገባቸው በአጠቃላይ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴያቸው በመጠንና በልክ ይሆናል፡፡

ሰሙነ ሕማማት ሲታሰብ አንድ ነገር እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመውደድ ከሰማይ ወደ ምድር መጣ፡፡ አይሁድ በገመድ ሲጎትቱት በፍቅር ተከተላቸው፡፡ አዳምን ግሩምና ድንቅ አድርገው የፈጠሩ እጆቹ በችንካር ተቸነከሩ፡፡ እፍ ብሎ የሕይወት እስትንፋስን የሰጠ ውቅያኖስን የፈጠረ አምላክ የሰዎችን ድምፅ ነፍስ ለማርካት ተጠማሁ አለ፡፡ ይህን የማያስብ ክርስቲያን ካለ በሕይወቱ የጎደለበት ቁልፍ ነገር አለ፡፡ ትዕቢተኛው ልብ የሚሰበረው በጥላቻ የተሞላ ኅሊና ጽሩይ የሚሆነው የክርስቶስ ፍቅር በልቡናችን ሲንጸባረቅ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ቢሆንም አምላካችን በሕማሙ፣ በሞቱና በትንሣኤው አምላካዊ ኀይል አድርጎ የሞትን ወጥመድ ሰብሮ ዲያብሎስን ሽሮ በሲዖል የነበሩ ነፍሳትን ነፃ አወጣቸው፡፡

በሰሙነ ሕማማት ከምንጸልያቸው ጸሎቶች መካከል “ለከ ኀይል፣ ክብር፣ ወስብሐት ወዕበይ ለዓለመ ዓለም…. ኀይል፣ ክብር፣ ምስጋና፣ ልዕልና ለአንተ ነው” የሚለው የምሥጋና ቃል ይገኝበታል፡፡

አምላካችን በመስቀል ላይ በመሰቀሉ ሞትን በመቅመሱ ደካማ እንዳናደርገው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው “በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቀን ለተስፋውም ቃል እንግዶች ሆነን በዚህ ዓለም ተስፋን አጥተን ከእግዚአብሔር ተለይተን” ኤፌ.2፥11-13 የነበረው ዘመን ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ በመሆኑም በተአምራቱና በቅድስናው፣ በአይሁድ እጅ በመያዙና ሞትን በመቀበሉ በመከራውና በመስቀሉ በትንሣኤው በምጽአቱ ሁሉ የመፍረድ የአምላክነት የሁሉን አድራጊነት ኀይል አለው፡፡

የጌቶች ጌታ የንጉሦችም ንጉሥ ራዕ.17፥14 በመሆኑ ልዕልና የእርሱ ነው፡፡ እርሱ ጸጋውን በውስጣችን አድርጎ በልባችን ዙፋን ተቀምጦ ሕይወታችንን እንዲመራ እንማጸነው፡፡  አምላክነቱን አውቀው ልባቸውን ያልሰጡትም በንስሓ እንዲመለሱ ብተ ክርስቲያን ትጸልያለች፡፡

ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም