ጉባያችን እንዲህ አለፈ
አጋዕዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት ገብተዉ ምግብ ተመግበው እንዲሁም የይስሃቅን መወለድ አብስረዉ የወጡበትን ዕለት የምንዘክርበት ለኛም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ስቶክሆልም ጉባዔ አስተባባሪ ኮሚቴ በጉጉት እና በደማቅ ዝግጅት ስንጠብቀው የነበረዉ ቀን ደርሶ እንዲህ በደማቅ እና ፍቅር በተሞላበት አገልግሎት አክብረነው አለፈ። እሁድ ሐምሌ 6 ጠዋት በደብሩ እና በእንግዶች ካህናትና ዲያቆናት በተአምረ ማርያም : በኪዳነ ጸሎት እንዲሁም በቅዳሴ ተጀመረ። ቅዳሴው እንዳበቃ ዕለቱን የሚያዘክር ያሬዳዊ መዝሙራት በህጻናት ጣፋጭ አንደበት ቀጥሎም በታላላቅ ወንድም እህቶቻቸዉ በሰንበት ተማሪዎች ቀረበ ። ሰዓቱ ወደ 10 ፡45 ገደማ ሲሆን በመምህር መጋቤ ሐዲስ ሚስጥረ ሥላሴ አባታችን አብርሃም በአምላክ ፊት ታዛዥ ታማኝና ትሁት ሆኖ በመገኘቱ ቅድስት ሥላሴ በጭንቀቱ ጊዜ በቤቱ ተገኝተው በበረከት እንደጎበኙት ፤ እንዲሁም የአንድነትና ሶስትነት ምስጢር እንደተገለጸለት ልብን በሚነካ ጥሩ አገላለጽ ካስተማሩን በኋላ እኛም መታመን የጎደለዉን ህይወታችንን ከአብርሃም በመማር እንዴት የአምላክን ጸጋና በረከት በህይወታች ን ማግኘት እንዳለብን ተረዳን። በዚህ ሰዓት በአስተባባሪ ኮሚቴ የምግብ እና መስተንግዶ ክፍል አባላት ሴቶች ማዕድ በማሰናዳት ሲሰማሩ በአንፃሩ ወንዶች በማስተናገድ ይተጉ ነበር ።
ከማዕድ መስተንግዶ በመቀጠልም ሰው ከሰው ጋር ሲኖር በፍቅር በመተሳሰብ በመከባበር እንዴት አብሮ መኖር እንደሚችል እንዲሁም በእምነት ስንኖር እንደ አብርሃም ለጋስ ልንሆን እደሚገባን የአብርሃምን አስራት ይዞ ወደ ካህኑ መልከ ጸዴቅ መሄድ በማስታወስ ነበር አባ ዘሚካኤል ትምህርታቸውን የጀመሩት። ቀጥለውም ምዕመኑም ትምህርቱን ተረድቶት ለመረዳት ከራሳቸው በመጀመር ለቤተክርስቲያን አስራት ማሰባሰብን ጀመሩ።
ለክፉ ቀን ደራሸ የሆነው ምዕመንም ትምህርቱ እንደ ገባው ሲያመለክት ለበረከት ይዞ የመጣው ሲሰጥ ያልያዘዉም ቃል በመግባት በጠቅላላዉ ወደ 80,000 ክሮኑር ተሰበሰበ ። የዲያቆናትና የካህናት አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነበር። ቀጥሎም ታቦተ ህጉ በዲያቆናትና በሰንበት ተማሪዎች ልዩ ዝማሬ በምእመናን እልልታና ጭብጨባ ታጅቦ ወደ ተዘጋጀለት ስፍራ ወጣ ። በመዘምራን በዓሉን የሚያዘክር ወረብ እና መዝሙር ከቀረበና አባ ዘሚካኤል ትምህርትና መልእክት በማስተላለፍ ካሳረጉ በኋላ የንግሱ ስነስርዓት ፍጻሜ ሆነ ።
እንዲህ እየደመቀ የተጋመሰዉ በአላችን አሁን ደግሞ ሰአቱ የመአድ መቁረስ ሆነና ምእመናን የተዘጋጀዉን የታፈጠ ምግብ እና መጠጥ በመስተንግዶ ክፍል አስተናባሪነት ተቋደሱ። በዚህ ግዜ የገቢ ክፍል አባላት በእለቱ የሚወጣ የእጣ ትኬት ይሸጡ ነበር ። በአባቶች የምስጋና ጸሎት የስጋን መብል አጠናቀን ወደ መንፈሳዊዉ ማእድ ተመለስን።
ያብርሃምና ሳራ ጋብቻ ያርግላችሁ ፦ በሚል ርዕስ በዲያቆን ደረጀ የትዳር ሂወታችን የነአብርሃምን ቢመስል እንዴት እንደሚባረክ ያብርሃምንና የሳራን ሂወት እያስቃኙ አስተማሩን ። በመዘምራን መዝሙር ቀርቦ የእለቱ የመጨረሻ ትምህርት በመምህር መጋቢ ሃዲስ ሚስጥረ ሥላሴ ስለ መቻቻልና መተሳሰብ ፤ የሃሳብ ልዩነት እንኩዋን ቢኖር በመሃላችን በፍቅር በመወያየት መለያየት ወደኛ እንዳይመጣ እንዴት እድንተጋ የአብርሃም እና ሎጥን ታሪክ አስዳሰው አስተማሩን።
በደብሩ አስተዳዳሪ አባ መላከ ብርሃን ሃይለ ጊዬርጊስ የእለቱን ጉባየ በተመለከተ ጠቅለል ያለ መልእክት እና ለእንግዶች ምስጋና አቅርበው የአምላካችን ቃል ለህልዉናችን እንደሚያስፈልገን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ቃሉን መስማትና መተግበር እንደሚገባ አስገነዘቡን። የተሸጠውን ትኬት እጣ ካወጣንና ለእለቱ እድለኞች ከተሰጠ በኋላ በጸሎት እና በአባ ዘሚካኤል ዝማሬ የእለቱ መረሃ ግብር ፍጻሜ ሆኖዋል ። ምእመናንም የተዘጋጀዉን ሻይና ዳቦ እየቀመሱ በደስታ እያመሰገኑ ለቀጣዩ ጉባዬ በቸር ያድርሰን እያሉ በረከታቸዉን ይዘው ወደየቤታቸዉ ሄዱ ።
እንደ በደላችን ሳይሆን እንደ ቸርነቱ በሰላም አስጀምሮ በሰላም ላስፈጸመን ክብርና ምስጋና አገልግሎት እና ውዳሴ ይሁን ለአብርሃሙ ሥላሴ !!!
ወስብሓት ለእግዚአብሄር፣
ከመስተግዶ ኮሚቴ