ዮም ተወልደ ቤዛ ኩሉ ዓለም

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!

ታህሳስ 28 ቀን 2007 ..

በመልአከ ብርሃን አባ ገብረ ጊዮርጊስ 

 

ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት።
ጊዜው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ።
 

Lidet

እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመጠበቁና ከፈጣሪው ፈቃድ በመውጣቱ ላለፈው ሥርየት፣ ለሚመጣው ዕቅበት ይሆነው ዘንድ ከኃጢኣቱ ከውድቀቱ ለማዳን ለዓለም ቤዛ  አንድያ  ልጁን ላከ። ይኸውም:-

  – በሥጋ በደም ይዛመደን ዘንድ፤ (እብ 2፥14፣ ዮሐ 6፥56-57)
    ”ውእቱኒ ተሳተፎሙ በዝንቱ” እንዲል
  – ያጠፋናትን ልጅነት በልደት መንፈሳዊ (በጥምቀት)
    ዳግም ይወልደን ዘንድ፤ (ዮሐ 3፥5-6 ቲቶ 3፥4-5)
  – የጠላትንም ምክር ያፈርስ ዘንድ፤ (ቆላ 2፥14 ኤፌ 2፥15)
  – ከልጅ ልጅህ ተወልጀ አድንሃለሁ ያለውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ፤

በቤተልሔም ተወለደ፤ወኮነ ከመ ሰብእ” – ”ሰው ሆነ። (ፍልጵ 2፥7)


ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ የማይታይ የማይዳሰስ ባሕርየ መለኮት በሚታይ በሚዳሰስ አካለ ትስብእት መጋረጃነት ተገለጠ። ዘበመንጦላዕተ ደመና ተሠወረ ወእምቅድስት ድንግል መድኅን ተወልደ” – ”በደመና መጋረጃ ተሰወረ፤ ከቅድስት ድንግል መድኅን ተወለደ፤ ጌታ ተገኘ፤ እውነተኛ ፀሐየ ጽድቅ ወጣ።እንዳለ ጎርጎርዮስ ዘሮሜ።

”ክብሩ ተለይቶት የነበረ ሥጋን ክቡር አምላክ ሊያደርገው የጸጋ ገዥነትን አጥቶ የነበረ ሥጋንም የባሕርይ ገዥ ሊያደርገው ወደደ፤ አዳም ከእኛ እንዳንዱ ሆነ ያለውንም ሰው በመሆን ሊገልጠው ወደደ።” በማለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሰው ልጅ በክርስቶስ ልደት ያገኘውን ክብር እና የእግዚአብሔርን ፍቅር ገልጧል  (ሃይ. አበው ም. 66 ቁ. 18)  እንዲሁም ”ሰው ያገኘውን፤ ልክ መጠን የሌለውን ፍጹም ክብር ከእግዚአብሔር የተደረገውን ባሕርያችን ያገኘውን ታላቅ ፍቅር አይቼ ከዚህ የተነሣ አደንቃለሁ” ብሏል። (ሃይ. አበው ም. 63 . 7) 

ከድንግል መወለዱም ድንቅ ነው። ናሁ ድንግል ትፀንስ ወኢይበሉ እፎ ትወልድ ከመ ይትነከር ልደቱ” – ”እነሆ ድንግል ትፀንሳለች እንዴት ትወልዳለች አይበሉ፤ ልደቱ ይደነቅ ዘንድ እንዴት ሆነ?” እያለ ይህ ፍጹም መምህር ዮሐንስ አፈወርቅ በአንክሮ እንደተናገረ። (ሃይ. አበው ም. 66 ቁ. 20)

ድንቅነቱ:- አምላክ ወሰብእ ሲሆን ባሕርዩ እንዳልተለወጠ እርስዋም እርሱን ስትወልድ ማኅተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ ነው። በኅቱም ድንግልና ፀንሳው በኅቱም ድንግልና ወልዳዋለችና። በዚህ ተዋሕዶው አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ በሚለው ትርጔሜ ስሙ አማኑኤል ተባለ። ወዝ ስም ዓቢይ ጥቀ ወኢይደሉ ፈሊጦቶ” – ይህ ስም ታላቅ ነው ሊለዩት አይቻልም። ተራ ሰው አይሉት አምላክ ነው፤ መለኮት ብቻ ነው አይሉት ሰው ነው። ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ በተዋህዶ የከበረ የአምላክነቱም የሰውነቱም ስም ነው። 

ስሙን ያወጣው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው ዘነበበ በነቢያት”:- “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል” – “እሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤”ብሎ ነቢያትን ያናገረ እርሱ ነውና። (ኢሳ 7፥14፣ ማቴ 1፥23) 

እንዲሁም እመቤታችንን ያበሰራት ክቡር መልአክወትሰምይዮ ስሞ ኢየሱስ” – ”ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” ብሏታል። ይህም ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነው። ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ” – ”የዓለም ሁሉ ቤዛ (መድኃኒት) ዛሬ ተወለደ” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ።

መልአከ እግዚአብሔርም ወደ እረኞቹ ሔዶ እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኁአለሁና እነሆ ዛሬ በዳዊት አገር መድኅን ተወልዶላችኁአል ይኸውም ቡሩክ አምላክ ክርስቶስ ነው። (ሉቃ 2፥10-11) በማለት አብስሯቸዋል:: እነርሱም የተወለደውን መድኃኒት ክርስቶስን አይተው ቅዳሴ መላእክትን ሰምተው፣ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” – ”ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” ብለው ዘምረው ሲመለሱ ያዩትን የሰሙትን ሰብከዋል። (ሉቃ 2፥12-18) 

እንግዲህ የሊቃውንቱም ሆነ የቅዱሳት መጻሕፍቱ ዋና ዓላማው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማመንና ማሳመን ነውይህ የተጻፈ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እናንተ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ የዘለዓለም ሕይወትን ታገኙ ዘንድ ነው። እንዳለ ዮሐ 20፥31 የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ትምህርት ሁሉ ይህን ማእከል ሊያደርግ ይገባል:- ኵላ መንፈስ እንተ ተአምን ከመ ኢየሱስ ክርስቶስ መጽአ በሥጋ ሰብእ እምነ እግዚአብሔር ይእቲ” – ”ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እንደ ሆነ የምታምን ትምህርት ሁላ ከእግዚአብሔር የተገኘች ናት” እንዲል 

እኛም ይህ በየዓመቱ የምናከብረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በብሉይም በሐዲስም በሊቃውንትም እንደተገለጠው እኛን ለማዳን ሲል በግርግም መጣሉን፣ በጨርቅ መጠቅለሉን፣ ፍቅሩን፣ ቸርነቱን፣ እያሰብን በሃይማኖት በምግባር ጸንተን የንስሓ፣ የፍቅር፣ የትህትና ፍሬን እንድናፈራ ነው። በሃይማኖት እኛን የማይመስሉትን ኑሮአችንን፣ በጎ ምግባራችንን፣ ሃይማኖታችንን፣ ፍቅራችንን አይተው በክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ሕይወታችን ለሌሎች ብርሃን እንዲሆንና እንዲሰብክ ያስፈልጋል። የማይኖሩበት ሕይወት እንኳንስ በእግዚአብሔር በሰውም ዘንድ ያስወቅሳልና በጎ ምግባራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ ብሎ ጌታ በወንጌሉ እንዳዘዘን እኛ መቅረዝ፣ ክርስቶስ ብርሃን ሆኖልን ልንኖር ይገባል። 

ስለ እኛ ሰው የሆነ መድኃኒት ክርስቶስ በዓሉን የሠላም የደስታ የበረከት ያድርግልን

አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

{flike}{plusone}