አእላፍ መላእክት

ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” ዕብ 1፥14

በአባ ገ/ጊዮርጊስ ካሳዬ

ኅዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም. 

”በዛቲ ዕለት አዘዙነ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ከመ ንግበር ተዝካረ በዓሎሙ ለአእላፍ መላእክት” – ”በዚች ቀን የአእላፍ መላእክትን የበዓላቸውን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተክርስቲያን መምህራን አዘዙን” የኅዳር አሥራ ሦስት ስንክሳር። 

አባቶቻችን መምህራን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው በሠሩልን ሥርዓት መሠረት ኅዳር አሥራ ሦስት ቀን የእልፍ አእላፋት መላእክትን የመታሰቢያ በዓል ቤተ ክርስቲያን ታከብራለች። ስለዚህም በዚህ አጭር ጽሑፍ የቅዱሳን መላእክትን የስማቸውን ትርጓሜ፣ ተፈጥሯቸውንና ለተፈጠሩበት ዓላማ ያላቸውን አገልግሎትበብሉይ ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳንና በሚመጣውም ዓለም የነበራቸውን፣ ያላቸውንና የሚኖራቸውን ድርሻ ባጭሩ እንመለከታለን።

1. የስማቸው ትርጓሜ

መላክ:- መሰደድ

ለአኪ:- የሚልክ፣ የሚሰድድ፣ ሰዳጅ – ”አመ ለአኩ ኅቤሁ አይሁድ” – ”አይሁድ ይጠይቁት ዘንድ በላኩ ጊዜ” እንዲል ዮሐ 1፥19

ተልእከ:- ተላከ፣ አገለገለ – ”ወተንሥአት ወተልእከቶሙ” – ”ተነሥታ አገለገለቻቸው” እንዲል ማቴ 8፥15

ተለአኪ:- የሚላክ፣ ተላላኪ፣ አገልጋይ

ልኡክ:- የተላከ፣ መልእክተኛ፣ አገልጋይ – ”ልኡከ እግዚእነ” – ”የጌታችን መልእክተኛ” 1ኛ ጴጥ 1፥1

”ግብረ ልኡካን” – የሐዋርያት ሥራ በቁሙ ”ግብረ ልኡካን” ይባላል።

ላእከ:- መልእክተኛ፣ አገልጋይ፣ ሎሌ – ”እስመ ላእካኑ እሙንቱ” – ”እነርሱ መልእክተኞች ናቸው” ሮሜ 13፥4

መልእክት:- በቁሙ መልእክት፣ ደብዳቤ – ”መልእክተ ዮሐንስ ሐዋርያ” – ”የሐዋርያው የዮሐንስ መልእክት” እንዲል 1ኛ ዮሐ 1፥1

መልአክ:- የእግዚአብሔር መልእክተኛ፣ ሰማያዊው፣ ረቂቁ የእሁድ ፍጥረት ይላል የአማርኛ ሰዋስው።

2. ተፈጥሯቸው

የመላእክት ተፈጥሮ ረቂቅ ነው፣ መናፍስት ናቸው፣ አይዳሰሱም፣ አይታዩም፣ ሥጋና አጥንት የላቸውም፣ አያገቡም፣ አይጋቡም፤ ይሕም ማለት በባሕርያቸው መራባት የለባቸውም ማለት ነው። ሉቃ 24፥39፣ ማቴ 22፥30። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮ ሁለት አይነት የአገላለጽ ዘይቤ አላቸው:- ”ግብር እምግብር” እና ”እምኀበ አልቦ”።

ግብር እምግብር ማለት ከተፈጠረው ከነፋስና ከእሳት ጠባይ ተፈጥረዋል የሚል ነው። ለዚህም መሠረት የሆነው በመዝ 103፥4 ላይ ”ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈስ ወለእለ ይትለአክዎ” – ”ነደ እሳት መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል” የሚለውን በመጥቀስ ነው።

እምኅበ አልቦ ለሚለው ደግሞ ”የመላእክት ተፈጥሮ ከማይመረመር ጠባይ ነው፤ የተፈጥሮ ባህርያቸው አይታወቅም፤ ከነፋስና ከእሳት ቢሆን ኖሮ ሞት በገዛቸው ነበር፣ አዳም በዚህ ጠባዩ ተፈጥሮ በሥጋው ሞት ገዝቶታልና” እንዳለ ታላቁ የቤተክርስትያን አባት ኤጲፋንዮስ ዘደሴተ ቆጵሮስ አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፉ። ስለሆነም የመላእክት ተፈጥሮ ከዚህ ነው ከማይሉት እግዚአብሔር ብቻ ከሚያውቀው ጠባይ ፈጥሮአቸዋል ብሏል። ”ወአልቦ ዘየአምር ባህርዮሙ ዘከመ እፎ ውእቱ እግዚአብሔርሰ የአምር ባህቱ” – ”የመላእክት ባሕርያቸው እንደምን እንደሆነ የሚያውቅ የለም እግዚአብሔር ብቻ ያውቃል እንጂ” እንዳለ ደራሲ። እግዚአብሔር መላእክትን በዕለተ እሑድ ፈጥሮ በሦስቱ ሰማያት:-በኢዮር፣ በራማ፣ በኤረር አስፍሯቸዋል (አክሲማሮስ)።

3. የቅዱሳን መላእክት ጥቅል ስም አጠራር

የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ ኢዮ 1፥6፤ መናፍስት ተብለው ይጠራሉ ዕብ 1፥14፤ ጠባቂዎች ተብለው ይጠራሉ ዳን 4፥7፣ ማቴ 18፥10፤ ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ ዘካ 14፣3፣ ማቴ 25፥31።

መላእክት በነገድ ዘጠና ዘጠኝ ናቸው ማቴ 18፥12 የአንድ ነገድ ቁጥሩና ብዛቱ በሰው ልጆች ሕሊና አይታወቅም። በጠቅላላው ”እልፍ አእላፋት ወትእልፊተ አእላፋት” – ብዙ የብዙ ብዙ በሚል ”የቁጥር የለሽ” አገላለጽ ይገለጻል እንጂ ግምት አይሰጠውም ዳን 7፥10፣ ዮሐ 5፥11።

በሥም ተለይተው ከሚታወቁት የቅዱሳን መላእክት ነገዶች መካከል ጥቂቶቹ ነገደ መላእክት፣ አጋዕዝት፣ ሥልጣናት፣ ኃይላት፣ መናብርት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፣ አርባብ፣ ኪሩቤል፣ ነገደ ሱራፌል ይገኙበታል። እነዚህም ነገዶች የእያንዳዳቸው የነገድ አለቆች ያሏቸው ሲሆን በስም ከሚታወቁት ጥቂቶቹ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል፣ ፋኑኤል፣ ራጉኤል፣ ኡራኤል፣ ሳቁኤል፣ አፍኒን ተጠቃሾች ናቸው።

4. አገልግሎታቸው

የቅዱሳን መላእክት ቀዳሚው አገልግሎታቸው የፈጠራቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው። ሲያመሰግኑም ”የመናፍስት ጌታ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ነህ፤ ፍጥረትህም ምድርን ይሞላል እያሉ ያከብራሉ፤ ያመስግናሉ፤ ከፍ ከፍም ያደርጋሉ” ኄኖክ 9፥39፣ ኢሳ 6፥2-4። እንዲሁም በዮሐ ራዕ 4፥11 እንደምናነበው ”ጌታችንና አምላካችን ሆይ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና በፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብርና ውዳሴ ኃይል ላንተ ይገባል” እያሉ የአማልእክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ የንጉሦችም ንጉሥ እግዚአብሔር አምላካችንን ያመሰግናሉ።

በሌላም ሥፍራ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ”አየሁም በዙፋኑ በእንስሶች በአለቆች ዙሪያ የብዙ መላእክት ድምጽ ሰማሁ ቁጥራቸውም የብዙ ብዙ እልፍ አእላፋት ነበር በታላቅ ድምጽ እንዲህ አሉ ለታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብና ብርታትንም ክብርና ምስጋናንም በረከትንም ሊቀበል ይገበዋል። በሰማይና በምድር ከምድርም በታች በባህርም ላይ ያለው ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለው ሁሉ በረከትና ክብር ምስጋናና ኃይልም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በዙፋኑ ለተቀመጠው ለበጉ ይሁን ሲሉ ሰማሁ” ራዕ 5፥11-14።

ቅዱሳን መላእከት ከምስጋና አገልግሎታቸው ቀጥሎ ለፍጥረቱ የፈጣሪያቸው የኃይሉ፣ የቸርነቱ የምህረቱ መገለጫዎች ናቸው። ይህ አገልግሎታቸው በተለይም በአዳምና በልጆቹ ጎልቶ ይታያል።

4.1. ቅዱሳን መላእክት አገልግሎት በብሉይ ኪዳን

አባታችን አዳም በፈጸመው ስሕተት ከገነት በተሰደደ ጊዜ በንስሐ ሆኖ በተስፋ እንዲጽናና ቅዱሳን መላእክት ይረዱት ነበር። ኄኖክም ስለቅዱሳን መላእክት አገልግሎት ”በዚያም ዐይኖቼ ከመላእክት ጋር ማደሪያቸውን፣ ከቅዱሳንም ጋር ማረፊያቸውን አዩ። ስለሰው ልጆች ይለምናሉ፣ ይማልዳሉ፣ ይጸልያሉም” ኄኖክ 9፥22-23 ሲል ተናግሯል። አባታችን ኖኅም ዓለም ለድምሳሴ በቀረበ ጊዜ በመርከብ ሥራው ይረዱት የነበሩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው። አበ ብዙኃን የተባለው አባታችን አብርሃም ከካራን በወጣ ጊዜ ጀምሮ የመላእክት ጥበቃ አልተለየውም፤ በመሆኑም ”ኢየቦር” የተባለ አገልጋዩን ወደ ሶርያ ወደ ባቱኤል ቤት በላከው ጊዜ ”የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል” በማለት ልኮታል ዘፍ 24፥7።

አባታችን ያዕቆብም ”ከሕፃንነቴ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ ያሳደገኝ የመገበኝ እግዚአብሔር መልአኩን ሰዶ ከመከራውም ሁሉ ያዳነኝ እሱ እነዚህን ሕፃናት ያክብራቸው” በማለት እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እንዳዳነው፣ እንደጠበቀው ያስረዳል ዘፍ 48፥16።

እስራኤልንም በመልአኩ መሪነት ወደ ምድረ ርስት መጓዛቸው ለሙሴ ተገልጾለታል ”በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወደ አዘጋጀሁልህ ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአኬን በፊትህ እልካለሁ ራስህን ጠብቅ ስማውም እምቢም አትበለው ስሜ በእርሱ ስለሆነ ይቅር አይልም” ዘጸ 23፥20-21።

እሥራኤል ዘሥጋ ምድረ ከነአንን ይወርስ ዘንድ ከግብፅ በወጣ ጊዜ መንገድ የሚመራውንና ምድሪቱን እስከሚወርስ ድረስ የሚጠብቀው መልአክ እንደታዘዘለት ሁሉ እሥራኤል ዘነፍስ የሆን እኛ ክርስቲያኖችም አሁንም መንገድ በተባለው ዕድሜአችንና ርስት የተባለችውን መንግስተ ሰማያት እስከምንወርስ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ የመላእክት ጥበቃ አይለየንም። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ”እስመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ይዕቀቡከ በኩሉ ፍናዊከ ወበእደዊሆሙ ያነሥኡከ ከመ ኢትትዐቀፍ በዕብን እግርከ” – ”በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለእናንተ ያዛቸዋል እግርህንም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሱሃል” መዝ 90፥11-12። መንገድ በተባለ በዚህ ዓለም የኑሮ ዘመናችን ሁሉ ይጠብቁን ዘንድ እግራችን በድንጋይ እንዳይሰናከል ማለት እግረ ኅሊናችን በኃጢአት፣ በዲያብሎስ ወጥመዶች እንዳንያዝ ይረዱናል። ”ከቶ ለማን ብሎአል ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ። ዕብ 1፥14።

ቅዱሳን መላእክት በእያንዳንዱ የኑሮ ተግዳሮቶች ሁሉ ጣልቃ ገብተው ይታደጉናል። ሎጥን ከጥፋት ከተማ፣ ያዕቆብን ከላባና ከኤሳው ቁጣ፣ ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ፣ ሠለሥቱ ደቂቅን ክእቶን እሳት ታድገዋል። ዘፍ 19፥1-22፣ ዘፍ 32፥1። የተራቡትን መግበዋል፤ ነቢዩ ኤልያስ ከኤልዛቤል ሸሽቶ በምድረ በዳ በረኃብ ደክሞ በተኛበት መልአኩ ምግቡን በአገልግል ወኃውን በመንቀል አቅርቦ መግቦታል 1ኛ ነገ 19፥5-7። ዳንኤልንም በቂሮስ ንጉስ ፋርስ ስድስት ቀን ሙሉ በአንበሳ ጉድጓድ በተጣለበት ጊዜ መልአኩ ዕንባቆምን በአንበሶ ች ጉድጓድ በባቢሎን ላለ ለዳንኤል ይህንን የያዝከውን ምግብ ውሰድለት ብሎት ከይሁዳ እስከ ባቢሎን መልአኩን ወስዶ አስመግቦ መልሶታል ዳን 14፥32-38።

የእግዚአብሔር መልአክ ሊያጠቁን ከሚመጡ የሥጋ ጠላቶችም ይታደጉናል፤ በዙሪያችንም አጥር ቅጥር ሆነው ይጠብቁናል ”የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል ያድናቸውማል” መዝ 33፥7፣ 2ኛ ነገ 6፥16-18።

4.2. የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት በሐዲስ ኪዳን

በሐዲስ ኪዳን መባቻ ላይ መላእክት የነበራቸው አገልግሎት የምሥራች ነበር። ለካህኑ ዘካርያስ ልደተ ዮሐንስን መልአኩ በምሥራች ነገረው ሉቃ 1፥11-17። ይኸው መልአክ ሥጋዌ ወልደ እግዚአብሔርን እንበለ ዘርአ ብእሲ ለምትወልደው ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በምስጋና አበሠራት። ሉቃ 1፥26-38። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በቤተልሔም መወለድ ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች ቅዱሳን መላእክት አበሠሩ። በጌታ ልደት ሰውና መላእክት ”ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” እያሉ በአንደነት ዘመሩ። ሉቃ 2፥8-20።

በጌታችን ትንሣኤም የምሥራቹ በመላእክት ታወጀ። ”ሕያውን ከሙታን መካከል ለምን ትፈልጋላችሁ እነሆ ተነስቷል” በማለት ሉቃ 24፥5። በጌታችን ዕርገትም ”እናንት የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል” የሐ ሥራ 1፥11። ”ለምን ቆማችኋል” በማለት የጊዜን ጥቅምና ወንጌልን ነገረ ምጽአቱን ለዓለም ሁሉ ይሰብኩ ዘንድ መክረዋቸዋል።

በስብከተ ወንጌልም መላእክት ተገቢውን ሥራ አከናውነዋል። አሁንም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እያከናወኑ ይገኛሉ። ቤተክርስቲያን መስፋት የቀኑ ካህናተ አይሁድና ሰዱቃውያን ሐዋርያትን በወህኒ አሳስረዋቸው የእግዚአብሔር መልአክ በሌሊት የግዞቱን ቤት ደጃፍ ከፍቶ አወጣቸው እንዲህም አላቸው ”ሒዱ ወደ ምኩራብም ግቡ፤ ለሕዝብም ይህንን የሕይወት ትምሕርት አስተምሯቸው” የሐዋ ሥራ 5፥19-20። ሄሮድስ አይሁድን ለማስደሰት ቅዱስ ጴጥሮስን ካሰረበት ወህኒ ቤት የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ጴጥሮስን) ከእስር ፈትቶ አውጥቶታል። የሐዋ ሥራ 12፥6-19።

ቅዱሳን መላእክት ሃይማኖት የጎደላቸውን ሰዎች ከአህዛብ ቤት ሳይቀር እንደነ ቆርኔሌዎስ ያሉትን ከሐዋርያት ጋር በማገናኘት እንዲጠበቁና ወንጌልን እንዲሰሙ ረድተዋል። የሐዋ ሥራ 10፥1-7። ከኃጢአትና ከበደል በንስሐ በሚመለሱ ምእመናን በሰማይ እጅግ ታላቅ ደስታ ያደርጋሉ። ሉቃ 15፥10።

4.3. የቅዱሳን መላእክት የዕለተ ምጽአት ርሻቸው

አምላካችን በግርማ መለኮቱ በክበበ ትስብእቱ በሚገለጥ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ከፊት ከኋላ ከግራ ከቀኝ ሆነው በክብር ይታያሉ። ”የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲገለጥ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ ይመጣል” ማቴ 25፥31። ሙታንም ይነሱ ዘንድ መላእክት መለከት ይነፋሉ 1ኛ ቆሮ 15፥52፣ 1ኛ ተሰ 4፥16። ”እነሆ ሙሽራው መጥቷልና ትቀበሉ ዘንድ ውጡ” እያሉ። ማቴ 25፥6።

በዚህ አለም ፍጻሜ እንዲህ ይሆናል የሰውልጅ መላእክቱን ያዛቸዋል በደል የሚያደርጉትንና ወንጀለኞችን ከመንግሥቱ ለይተው ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት ይጨምሯቸዋል ማቴ 13፥41-42። በጎ የሚያደርገውን ሊያበረቱ ክፉ አድራጊውን ሊቀጡ እግዚአብሔር የሾማቸው ሰለሆነ። ሮሜ 13፥ 4።

ቅዱሳን መላእክት በሰው ልጆች ኑሮና ዘመናት ሁሉ ከከፉ መጠበቅ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ሕይወታችን መንገድ በመምራት እንደጠባቂነታቸው (ማቴ 18፥10)፤ ለሰው ልጆች እድሜንና የንስሐ ዘመን እንዲሰጠን በአምላካቸው በእግዚአብሔር ፊት በመጠየቅ (ሉቃ 13፥6-9) ይማልዱልናል።

እኛም እንዳባቶቻችን:-

”ሰአሉ ለነ መላእክት ቅድመ መንበሩ ለጸባዖት” – ”ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር አምላካችን ፊት ለምኑልን፣ አማልዱን፤ 

”ነገደ መላእክት ፺ወ፱ቱ … ምህላነ አእርጉ ለለዕለቱ” –  ”ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ምህላችንን በየዕለቱ አሳርጉልን”፤

”ሰአሉ ለነ ማኅበረ መላእክት ፍሡሓን እለ ኢትነውሙ ትጉሃን እንበለ አፅርዖ ሰባሕያን።” – ”ደስ የተሰኛችሁ፣ በትጋት ያለእረፍት የምታመሰግኑ ማኅበረ መላእክት ለምኑልን” እያልን በአማላጅነታቸው እንማጸናለን።

የአእላፍ መላእክት ጥበቃቸው፣ አማላጅነታቸው፣ ረድኤት በረከታቸው አይለየን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

{flike}{plusone}