የኪዳነምሕረት በዓል አከበሩ
በመ/ጸ/ቅ/ስ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤት ታዳጊዎች አመታዊ የኪዳነምሕረት በዓል አከበሩ
የካቲት 11 ቀን 2009 ዓም የኪዳነምሕረት ማህበር አባላት ወይንም የቤተ ክርስትያኑ ሰንበት ት/ቤት ታዳጊዎች በደመቀ ሁኔታ አመታዊ የኪዳነምሕረትን በዓል አክብረዋል። የአገሪቱ ሁኔታ የኪዳነምሕረትን በዓል በቀኑ ለማክበር አስቸጋሪ ቢያደርገውም የማህበሩ አባላት ቀደም አድርገው ቅዳሜ ቀን የካቲት 10 ላይ በሰፊው አክብረዋል። በአሉንም በደብሩ አስተዳዳሪ በአባ ገብረ ጊዮርጊስ ጸሎትና ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን፤ በዝግጅቱም ላይ በታዳጊዎች የተዘጋጁ ግጥም፣ ጭውውት፣ ድራማና ታሪክ እንዲሁም ውዳሴ ማርያምን በዜማ ቀርቧል።
ለታዳሚው ጥሩ መልክት ካስተላለፉት መካከል በድራማ መልክ የቀረበው ከሞት ጋር የተደረገ ውይይት የሚለው አንዱ ነበር በድራማው ላይ ሞት ስለትውልድና ዕድገቱ ሲጠየቅ የሚከተለውን ብሎ ነበር ̋አያቴ ምኞት፤ አባቴ ቃየል፤ እናቴ ደግሞ ሐጢያት ይባላሉ። የተወለድኩት 5500 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው ከዚያ ወዲህ በመላው ዓለም እየተዘዋወርኩ የሰውን ልጅ ከዚህ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ሳጐዘው እኖራለሁ ̋፟ ብሎ መልሶ ነበር፣ በተጨማሪም የስሙ ትርጉም፣ የት እንደሚኖር፣ የተደሰተባቸው ቀናት፣ ዛሬ በምን እንደሚደሰት፣ ስለ ወገኖቹ፣ ሰዎችን እንዴት እንደሚመለከታቸው፣ ሰዎች ለምን እንደሚፈሩት እናም ስለ አስቂኝ ገጠመኞቹ በድራማው ተዳስሰው ነበር።
ስለ ታቦት በቀረበው ጭውውት ላይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ እና መናፍቅ ያደረጉትን ውይይት ስለ ታቦት ምንነት በዝርዝር እና በደንብ አስተምረዋል። ስለቅዱሳን ታሪክ በመነባንብ መልክ የአባ ኢየሱስ ሞዓ ወይንም የመጀመርያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ዩኒቨርሲቲ መሥራች ታሪክ ተተርኳል። እንዲሁም በጣም አስደሳች እና አስገራሚ የነበረው የህፃናት ሃይማኖታዊ ጥያቄና መልስ ውድድር ተካሂዶ ሁሉም ህፃናት ምንም ጥያቄ ባለመሳሳት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ወስደዋል።
በመጭረሻም ከታዳሚዎች ገንቢ አስተያየትን ለማሕበሩ አባላት ተሰጥቶ የፕሮግራሙ መጠናቀቂያ ሆኗል።