የትንሣኤው ትርጉም በዓሉና አከባበሩ
ከሊቀ ትጉሃን ኀ/ጊዮርጊስ ዳኘ
በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ምክ/ሓላፊ
-
«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡
-
መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
-
«ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
-
«ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡
-
«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡
-
መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
-
«ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡
-
«ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡
-
አንደኛው «ትንሣኤ» ኅሊና ነው፡፡ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር ነው፡፡
-
ሁለተኛውም «ትንሣኤ» ልቡና ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡
-
ሦስተኛው «ትንሣኤ» ለጊዜው የሙታን በሥጋ መነሣት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል፡፡
-
አራተኛው «ትንሣኤ» የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ የእርሰ ትምህርታችንም መሠረት ይኸው እንደሆነ ይታወሳል፤ ብለን ተስፋ አናደርጋለን፡፡
-
ዐምስተኛውና የመጨረሻው «የትንሣኤ» ደረጃም የባሕርይ አምላክ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «ትንሣኤ» መሠረት ያደረገ «ትንሣኤ ዘጉባኤ» ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡
-
ወደተነሣንበት ዐላማ ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በቃሉም ምስጢር በይዘቱም ስለሚመሳሰሉ ጥላው ምሳሌውም፣ ስለሆነ «ፋሲካ» ተብሎ ይጠራል፡፡
-
«ፋሲካ» ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ፌሳሕ» በጽርእ በግሪክኛው «ስኻ» ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ ዕድወት = ማዕዶት፣ በዓለ ናእት = የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ነጮቹ በእንግሊዝኛው «ስኦቨር» ይሉታል የዚህም ታሪካዊ መልእክቱ በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓል «ትንሣኤ» ተተክቶበታል፡፡
-
ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ምእመናነ ክርስቶስ ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በእርሱ ትንሣኤ
-
ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣
-
ከኀሳር = ከውርደት ወደክብር፣
-
ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣
-
ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲሰ ሕይወት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡
– መድኀኒታችን ሞትን በሞቱ ድል መትቶ፣ ስሙና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ የተነሣው መጋቢት 29 ቀን በ34 ዓ.ም እንደሆነ ታሪከ ቤተ ከርስቲያን ያስረዳል፡፡
– የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው በተነሡት ተከታዮቹ ምእመናን ነው፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዐቱ ይበዛ ይቀነስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ተቋርጦ አያውቅም፡፡ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን»
– ሲወርድ ሲወራረድ ከዚህ በደረሰው ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሕማማቱን ስታነብ ሰንብታ ለትንሣኤ እሑድ አጥቢያ ማታ በ2 ሰዓት «ለጸሎት ተሰብሰቡ» የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡
– ካህናቱ ተሰብስበው ሥርዐቱን በጸሎት ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም ይሰበሰባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንም ይሞላዋል፡፡
– ካህናቱ ሁሉ ለጸሎተ ፍትሐትም፣ ለሥርዐቱም መዝሙረ ዳዊት፣ ነቢያት፣ ሰሎሞንና ውዳሴ ማርያም ከደገሙ በኋላ «ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ» የሚለውን ግጥማዊ የደስታ መዝሙር ይዘምራሉ፡፡
– ሕዝቡም የቻለው በዝማሬው ያለበለዚያም በጭብጨባና በልልታ የደስታ ዝማሬው ተሳታፊ ይሆናል፡፡ ይህ ምስባኩ በዲያቆኑ 2 ጊዜ በመላው ካህናትም 2 ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ዲያቆኑም መላው ካህናትም አንድ ጊዜ ብለው 5 ጊዜ ይሆናል፡፡ 5500 ዘመን ሲፈጸም በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ዓለም ለመዳኑ ምሳሌያዊ ማስረጃ ነው፡፡
– አሁንም ካህኑ «አሰሮ ለሰይጣን = ሰይጣንን አሰረው» ባለ ጊዜ መላው ካህናት «አግዐዞ ለአዳም = አዳምን ሐርነት ነጻነት አወጣው» ይላሉ፡፡ ቀጠል አድርጎ ቄሱ «ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት» ሲላቸው ሁሉም ካህናት «እምይእዜሰ = ከዛሬ ጀምሮ» ብለው ይቀበላሉ፡፡ ቄሱም «ኮነ ፍሥሐ ወሰላም = ሰላምና ደስታ ሆነ» ብሎ ሦስት ጊዜ ዐውጆ ሲያበቃ «ነዋ መስቀለ ሰላም» እያለ መስቀል ሲያሳልም ካህናትና ሕዝቡም «ዘተሰቅለ ቦቱ መድኀኔዓለም» እያሉ ይሳለማሉ፡፡ ካህኑም «እግዚአብሔር ይፍታ» ይላል፡፡ ግብረ ሕማማት ሲነበብበት ከሰነበተው ጠበልም ይረጫል፡፡ የተረፈውንም ጠበል ሕዝቡ ለበረከት ወደየቤቱ ይወስደዋል፡፡
– ከዚያም ልኡካኑ ለቅዳሴ እየተዘጋጁ ሊቃውንት መዘምራኑ ምስማክ መወድሱን ካዜሙ በኋላ በመቋሚያ ይዘምሙታል፡፡ አያይዞም በዓመት ሦስት ጊዜ የሚዘመረውን «ይትፌሣሕ» የተባለውን መዝሙር ቃኝተው ከዘመሙ በኋላ «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ = ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካውን ታደርጋለች፡፡» እያሉ ይጸነጽላሉ፡፡ አያይዘውም የመዝሙሩን ሰላም ይጸፋሉ፡፡
– ወዲያው መንፈቀ ሌሊት ሲሆን ቅዳሴ ተቀድሶ ይቆረባል፡፡ ከዚያም ዕጣነ ሞገር = በዕጣን ፈንታ ቅኔው ተቁሞ ሠርሖተ ሕዝብ = የሕዝብ ስንብት ከሆነ በኋላ ለመፈሰክ ሕዝቡ ወደየ ቤቱ ይሔዳል፡፡
– ሕዝቡ በየቤቱ፣ ካህናቱም ከቤተ ክርስቲያን በየአካባቢው ባህል በተለይ አክፋዮች መጀመሪያ ቅባት አጥቶ የሰነበተ ሆድ እንዲለሰልስ የተሞቀ የተልባ ጭልቃ ይጠጣና የሹሮ ወጥ በቅቤ፣ በአይብ፣ የበረታም በዶሮ ወጥ፣ ወይም በበግና በከብት ሥጋ ወጥ ይገድፋል፡፡
– በእርጎ፣ በአይብ የተደራረበ እንጀራ በግፍልፍል የሚገድፉም አሉ፡፡ በአንዳንድ የሰሜኑ ሀገራችን ደግሞ የተልባ፣ የኑግና የሱፍ ጭልቃ ከማር ጋር ታሽቶ ከተጠጣ በኋላ በእርጎ፣ በአይብ፣ በወተት፣ በቅቤና ድልህ በተቀባ እንጀራ ይገድፋሉ፡፡
– ሲነጋም ከጾሙ አጋማሽ ጀምሮ ወንዱ ለእርድ የሚሆነውን ሰንጋውን፣ ሲቀልብ፣ በጉን ፍየሉን ሲሞክት ዶሮውን ሲመርጥ፣ ሲገዛ ሲለውጥ፣ ሰንብቶ ነበርና በግልም በኅብረትም ያ ይታረዳል፡፡
– ሴቶችም ቅቤውን ሲያነጥሩ፣ በርበሬውን ሲደልሁ፣ ለእንጀራና ዳቦ የሚሆነውን ዱቄት ሲያዘጋጁ ለጠላ የሚሆነውንም እኸል ሲያሰናዱ አይቡን በልዩ ልዩ ቅመም መጣጣ ሲያደርጉና ባዶ ማለትም ወገሚት የተባለውን በሽንኩርት፣ በጤና አዳም፣ ጣዕሙ እንዳይለወጥ ሲቀምሙ ሰንብተው ዝግጅቱ ተከናውኖ ነበር፡፡
– ጧትም ይህ የመግደፊያ ዝግጅት በየቤታቸው ለሌላቸው ድኾች በየመንደሩ እየተዞረ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ» እየተባለ ከሥጋውም፣ ከአይቡም፣ ከቅቤውም ከመጣጣሙም፣ ከእርጐውም ይታደላል፡፡
– ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ» እየተባባለ በመጠራራት ዐብሮ ሲበላ ሲጠጣ ልዩ ልዩ ጨዋታ ሲጨዋወት ለንስሐ አባትና ለሽማግሌዎች ለወዳጅ ዘመድም የአክፋይ ዳቦ፣ ወይም የሥጋ ወጥ ግፍልፍል ሲወስድ ይሰነብታል፡፡
– ማክሰኞ = የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ሐዋርያ አልነበረም ኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት እኔ ሳላይ አላምንም በማለቱ በዚህ ጥያቄው መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ ሆና ዕለቲቱ «በቶማስ» ተሰየመች፡፡ ዮሐ. 20-24-30
– ረቡዕ = ከሞተና ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላሥነሣው፣ አላዓዛር መታሰቢያ የእርሱንም ተነሥቶ በማየት በጌታችን ብዙ ሕዝብ ስለአመነበት ቀኒቱ «አላዓዛር» ተብላ ትታሰባለች፡፡ ዮሐ. 11-38-46
– ኀሙስ = ከላይ በጸሎተ ኀሙስ ሐተታ ላይ እንደተገለጸው የአዳም ተስፋው ተፈጽሞለት ከነልጅ ልጆቹ ወደቀደመ የገነት ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆና «የአዳም ኀሙስ» ተብላ ይኸው ትከበራለች፡፡ ሉቃ. 24-25-49
– ዐርብ = በክርስቶስ ደም ተዋጅታ በተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ በመሆኗ በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ዐርብ «ቤተ ክርስቲያን» ተብላ ትጠራለች፡፡ ማቴ. 26-26-29 የሐ. ሥራ. 20-28 ይህች ዕለትም እንደ ዕለተ ኀሙስ ሦስት ስያሜዎች አሏት፡፡ ይኸውም እንደኛው ከሆሳዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ የጌታችን አርብዓው ጾም የሚፈጸምባት የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት፣ በመሆኗ በቤተ ክርስተያን «ተጽዒኖ» ስትባል በሕዝቡም ዘንድ በሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤው ከባዱን ሥራ ስለሚያቆምባት «የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ» ትባላለች፡፡
– ሦስተኛውም ይኸው በሰሙነ ትንሣኤው ያለችው ደግሞ «ቤተ ክርስቲያን» ትባላለች ማለት ነው፡፡
– ቀዳሚት = በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበይባት «የቁራ ገበያ» የገበያ ጥፊያ ስትባል በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ለአገለገሉት በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት፣ የትንሣኤው ዕለት ገና ከሌሊቱ ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው በመገሥገሣቸው ትንሣኤው ከሁሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አእንስት መልካም መታሰቢያ ሆና «አእንስት» ተብላ ትጠራለች፡፡ ሉቃ. 23-27-33፣ 24-1-01፣ ማቴ. 25-1-11
የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ…
– በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሁሉ ከቅዳሴው ውጭ ከሚፈጸመው «ድኅረ ቁርባን» በስተቀር ልክ እንደመጀመሪያው የትንሣኤ ዕለት ሆኖ ይከናወናል፡፡
ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን፡፡ አሜን!!