ለየካቲት 23 2006 ዓ.ም. (March 2, 2014) በ Vårby skolan ይካሄዳል ተብሎ የተጠራውን ስብሰባ ሀ/ስብከቱ እውቅና የማይሰጠው መሆኑን ገለጸ

እንደሚታወቀው በምእመናን እና በቤተ ክርስቲያኑ የቀድሞ የሰበካ አስተዳደር መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና በአስተዳደሩ በተወሰደው ቤተ ክርስቲያንን የማሸግ ኢ-ቀኖናዊ እርምጃ ላይ መፍትሄ ለመስጠት የሰ/ም/አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና ዋና ሥራ አስኪያጁ ከአንድም ሁለት ጊዜ ወደ ስቶክሆልም መምጣታቸው ይታወሳል። በእነዚህ ሁለት አበይት ስብሰባዎች የቀድሞው የሰበካ አስተዳደር የሀገረ ስብከቱ ከፍተኛ ልዑካን እና ምእመናን በተገኙበት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን እንዲያስረዱ በተደጋጋሚ በደብዳቤ፣ በስልክ፣ በኢሜል ቢጋበዙም ለመገኘት ፈቃደኛ አልሆኑም። ስለሆነም የምእመኑን መንፈሳዊ አገልግሎት የማግኘት መብትና የቤተ ክርስቲያኑን ደህንነት ለማስከበር ሲባል የካቲት 02 ቀን 2006 ዓ.ም. በ S:t Jacobs Kyrka, Stockholm , Sweden በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ የሰበካ አስተዳደር ኮሚቴ ተመርጧል።

ይሁን እንጅ ከላይ በተገለጸው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለተመረጡት አዲስ የሰበካ አስተዳደር ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኑን ንብረት ማስረከብ ሲገባ በተቃራኒው ያለ ሀገረ ስብከቱ እውቅና እንዲሁም ምእመኑ የመረጠውን አዲስ የሰበካ አስተዳደር ኮሚቴ ስልጣን በመጋፋት የቀደሞው አሰተዳደር ለየካቲት 23 2006 ዓ.ም. (March 2, 2014) በ Vårby skolan, Vårby allé 26-30, በህገወጥ መልኩ የሀገረ ስብከቱን እና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስም በመጠቀም ምእመኑን ለስብሰባ መጥራታቸው በተለያየ መንገድ ከበተኗቸው የጥሪ ማስታወቂያዎች ለማየት ተችሏል። ይህን ሕገ ወጥ ተግባር በምእመናን የተመረጠው አዲሱ የሰበካ አስተዳደር ኮሚቴ ለሀ/ስብከቱ አሳውቋል። ይህን ተከትሎም ሀገረ ስብከቱ ይህን ስብሰባ እንደማያውቀውና እውቅናም እንደማይሰጠው በላከው ደብዳቤ አሳውቆናል።
በሌላ በኩል በቀድሞው የሰበካ አስተዳደር አባላት ጠያቂነት ከቅዱስ ፓትርያርኩ በተላለፈ መመሪያ መሠረት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለቀድሞው የሰበካ አስተዳደር ሶስተኛ ዕድል ለመስጠት እና ያለውን ችግር በሰላም እና በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት ለመፍታት ይልቁንም የእርቅ ጉባኤ ለማካሄድ ለመጋቢት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ስቶክሆልም እንደሚመጡ በደብዳቤ ለቀድሞው አስተዳደር አባላት እና ለእኛም በግልባጭ አሳውቀውናል።

{gallery}gal_letters,width=190,height=190{/gallery}በመጫን ደብዳቤዎቹን ያንብቡ

የቤተክርቲያናችንን ሕግ እና ሥርዐት መጠበቅ እና ማስጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት በመሆኑ ምእመናን በሙሉ ይህ የተጠራው ስብሰባው በምእመናን መካከል ክፍፍልን የሚፈጥር እና ለቤተክስቲያኒቱም ሰላም የማይበጅ መሆኑን ተገንዝባችሁ በእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ተባባሪ ከመሆን እንድትቆጠቡ በአክብሮት እናሳስባለን።

ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክስቲያናችንን ሰላም ይጠብቅልን

{flike}{plusone}