ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት

 
በዓቢይ ጾም ከሰርከ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፤ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለመሳሳም፤ አክፍሎት፤ ቄጤማ ማሰር፤ ጥብጣብ፤ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለ እነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈጻጸም መዛግብት አገላብጠን፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አለመሳሳም፡-
በሰሙነ ሕማማት ምእመናን መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፤ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡
 
ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንስቀለው . . . እንግደለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያንን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፤ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡
ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ እኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው፤ ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት /የተቀደሰ ስጦታ/ አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሄዋንን ሰላም ለኪ ብሎ ነው ያታለላት፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት የሰላምታ ልውውጥ አይደረግም፡፡
ሕጽበተ እግር፡-
የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት፤ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው፡፡
ሕጽበተ እግር ጌታችን እናንተ ለወንድማችሁ እንዲህ አድርጉ በማለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ
/ዮሐ.13፡16-17/ በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡
ጌታ በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር ሲያጥብ እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአያን ሰጥቻችኋለሁ፤ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል አለ፡፡ ደቀመዛሙርቱም ማን ይሆን? አሉ፡፡ ጌታም ኅብስት ቆርሼ፤ ከወጡም አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው አላቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱም ደነገጡ፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ነበር፤ ለጊዜው ግን አልገባቸውም፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመስጠት የኦሪትን መስዋዕት የሻረው እና መስዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ ትኩሴ፤ በጎንደር ደግሞ ሙገራ ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸውን ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፡፡ በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡
በሰሜን ወሎ ሀገረ ስበከት በቅዱስ ላሊበላ አጠገብ በሚገኘው የይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጣርያ ላይ ካህኑ ትኩሴ ዳቦ ሲባርክ የሚያሳይ ሥዕል አለ፡፡
በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ጸጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ ኃጢአት ይሆንበታል ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል የለም፡፡ ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን እንግልትና መስቀል ለማዘከር ነው ተብሎ ይነገራል፡፡
እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት አባቶች በያሉበት አጥቢያ /ደብር/ በመገኘት በመዓርግ የሚያንሷቸውን የካህናት፤ የዲያቆናት እና የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ የሚያጥቡትም የወይራና የወይን ቅጠል በውኃ በመዘፍዘፍ ነው፡፡
አክፍሎት፡-
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከአርብ እስከ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ብዙዎች ያከፍላሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፤ ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡
ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬኔዎስ፤ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፤ ሐዋርያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ እና ከትንሽ ውኃ በቀር እንደማይመገቡ፤ ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉም ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኸው ነው፡፡
ጉልባን
ጉልባን ከባቄላ ክክ፤ ከስንዴ ወይም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም አብዛኞቹን የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይታሰባል፡፡
ጥብጣብ፡-
በሰሙነ ሕማማት ዕለት ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማት ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ፤ ሲጸልይ፤ ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ /የሕዝብ መሰነባበቻ/ ከመሆኑ በፊት በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባ ቸብቸብ መደረጉ የጌታን ግርፋት ለማሰብ ነው፡፡ ማቴ.27፡26፤ 19፤1-3/
ቄጤማ፡-
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላም እንደሰጠን እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ገጸ በረከት ያቀርባሉ፤ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡
በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው፤ ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቁ ምእመናን ትልቅ ብስራት ነው፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፤ ከሚያዝያ 1-5 ቀን 2004 ዓ.ም.
 
{flike}{plusone}